Tuesday, May 18, 2010

ዝምታህ ጮኸብኝ!

አንተ ፀጥ ያልከው ሰው- አንት የተሎጎምከው
አጥርህ ዙሪያ ታጥሮ- በርክን የዘጋኸው
ሰው መሃል ሆነህ- ከሰው ልጅ የራከው
ለምስጋናም አሜን
ለእርግማንም አሜን
አሜን በፀጥታህ- አሜን አሜን ያልከው
ዝምታህ ጮኸብኝ- ጆሮየውን በጠሰው
እባክህ ተናገር- ዝምታህም ያብቃ
ዝምታ ትብብር- ከበዳይ አለቃ
መሆኑን እወቀው- የዝምታ ደሞዝ
ዝምታ ጠላት ነው- ይኸን እወቅ ጎበዝ።

ነጎድጓድ ባልሰማም- የመብረቅ ብልጭታ
የአውሎ ነፋስ ጩኸት- የዝናብ እሩምታ
መርዶን- ተከትሎ- ደረት ባይመታ
“ወየው ወይኔ!” ባይኖር እንባም መንታ መንታ
ዝምታ ረብሻ ነው- ከጩኸት የበዛ
ህሊናን በጭንቀት- ሰው በአሳር የገዛ።

አወይ ገለልተኛ- አወይ ትርምሱ- አወይ ግሳንግሱ
የዝምታ ጓዙ- በየትኛው ድልድይ- ይሻገራል እሱ
ከእኛ እሚባል እኛ- አሻግሮ የሚያይ ጠፍቶ
ልዩነት ይታያል-ከአንድነቱ ጎልቶ
አወይ ገለልተኛ- ምነዋ አንናገር- አንደበት ተዘጋ
ለአገራችን ጉዳይ- ማንስ ለእኛ ያውጋ
ምነው ዝም የምንል- ህዝብ እየተወጋ?

አሜን በፀጥታህ- አሜን አሜን ያልከው
ዝምታህ ጮኸብኝ- ጆሮየውን በጠሰው
እባክህ ተናገር- ዝምታህም ያብቃ
ዝምታ ትብብር- ከበዳይ አለቃ
መሆኑን እወቀው- የዝምታ ደሞዝ
ዝምታ ጠላት ነው- ይኸን እወቅ ጎበዝ።


ዳግማዊ ዳዊት
ግንቦት 2002 ዓ.ም.
Ethio_dagmawi@yahoo.com

No comments: